ቡና በኮረንቲ ከደበነ
ቡና በኮረንቲ ከደበነ፤
ባንድ ፍንጀል ከወሰነ፤
ምኑን ቡና ሆነ!?
ቡና ይሏችኅል ከተቆላ፤
እስከ ሶስተኛ የሚፈላ!!!!
አጀቦት ሲኒ_’ረከቦት _’ጀበና፤
ወይራ -እጣን -በጊርጊራ ፤
እንጂ ምኑን ተባለ ቡና!?
ፉት ሲሉ ካንዱ ሰም ጋር፤
ካልገባበት አንድ ስካር፤
ጭልጥ – ከናስሩ ምክር፤
ካለማጉ – ከሰው ትዳር፤
ቡና ያኔነው የ’ሚያምርው።
ፈንድሻ ቄጠማ ተነስንሶ፤
እንደ ቁርስ -ሃሜት ነክሶ፤
ካላቆየ ፍቅር ከሶ፤
ምኑ ቡና ውግ አፍርሶ!!!
ያሽሙር እጣን ካልተመመ፤
ቁርሾ አቡክቶ ካልተመመ፤
ቀናው ነገር ካልጠመመ፤
በመን ወጉ ቡና ጣመ።
ያቡና አተላው ሲፈስ፤
ካልበተነ በጣብ ድግስ፤
አኮራርፎ ካልመሸገልን–
ሸንጎው ለነገ ካልተቀጠርን፤
ቡና አይባለም ይሆናል ቡን።
ስዩም ተፈራ
ከሶስቱ እንባዎች ያተወሰደ